ዝንጀሮው ኮኮ ከሚወደው የማንጎ ዛፍ ላይ ተንሸራቶ ወረደና ዛሬ ቀኑ ነው ብሎ ጮኸ። የምኑ ቀን ስትል ፍየሏ ቲቲ እየጋለበች መጣችና ጠየቀችው። በዛፉ ላይ ካሉት ሁሉ ትልቁን ማንጎ የምበላበት ቀን ነዋ! አለ ዝንጀሮው ኮኮ። ኮኮ ከቅርንጫፉ ላይ ተንጠልጥሎ ወደነበረው በጣም ትልቅ ወርቃማ ማንጎ ወደ ላይ እጁን ቀስሮ አሳ

Created in Canva

በአንድ ትልቅ ጫካ ውስጥ፣ ከሚያብረቀርቅ ወንዝ አጠገብ፣ በቀለማት ባማሩ የዱር አበቦች ተከብቦ፣ አንድ ተጫዋች ትንሽ ጦጣ እና የቅርብ ጓደኛው የሆነች ደስተኛ ትንሽ ፍየል ይኖሩ ነበር። ጦጣው ዛፎች ላይ መንጠላጠል እና ከቅርንጫፍ ቅርንጫፍ መዝለል በጣም ይወድ ነበር። ሁለቱ ጓደኞች ሁሉንም ነገር ማለት ይቻላል አብረው ያደርጉ ነበር። ቢራቢሮዎችን ያሳድዱ ነበር። ዓሦች በወንዙ ውስጥ ሲፈነጩ ይመለከቱ ነበር። በሙቀት ሰአት በማንጎ ዛፎች ቀዝቃዛ ጥላ ሥር ያርፉ ነበር። ከሁሉ በላይ ግን ውብ መኖሪያቸውን ማሰስና አዳዲስ ነገሮችን ማግኘት ይወዱ ነበር።

አንድ ቀን በጠዋት ዝንጀሮው ኮኮ ከሚወደው የማንጎ ዛፍ ላይ ተንሸራቶ ወረደና "ዛሬ ቀኑ ነው" ብሎ ጮኸ። "የምኑ ቀን?" ስትል ፍየሏ ቲቲ ጠየቀችው። በዛፉ ላይ ካሉት ሁሉ ትልቁን ማንጎ የምበላበት ቀን ነዋ! አለ ዝንጀሮው ኮኮ። ከቅርንጫፉ ላይ ተንጠልጥሎ ወደነበረው በጣም ትልቅ ወርቃማ ማንጎ ወደ ላይ እጁን ቀስሮ አሳያት። ቲቲ ወደ ላይ ቀና ብላ አይታ "በእርግጥ በጣም ትልቅ ማንጎ ነው። ካንተ የሚበልጥ ይመስለኛል" አለችው። "ልክ ነሽ ከእኔ ይበልጣል! በማንጎ ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም ጣፋጭ ማንጎ ይሆናል።" ብሎ ኮኮ ፈገግ አለ።

በማግስቱ ጠዋት ኮኮ ጅራቱን እያወዛወዘ ወደ ዛፉ እየሮጠ ሄደ። ከዚያም ባየው ነገር ደንግጦ "ወይኔ!" አለ። ቲቲ እየሮጠች መጥታ "ምንድን ነው?" ብላ ጠየቀች። "ማንጎዬ!" ብሎ ኮኮ ወደ ላይ እየጠቆመ ጮኸ። ቅርንጫፉ ሙሉ በሙሉ ባዶ ነበር። ማንጎው ጠፍቷል። ቲቲ በድንጋጤ ትንፋሽ ስላጠራት ልትወድቅ ምንም አልቀራትም። "ጠፋ?!" አለች። ሁለቱ ጓደኛሞች በሀዘን ባዶውን ቅርንጫፍ እያዩ ሳይንቀሳቀሱ ቆሙ።

"ወድቆ ይሆን? እስኪ በየቦታው እንፈልገው።" አለች ቲቲ። ከዚያም ኮኮ ከቅጠሎች በታች እና ከድንጋዮች በስተጀርባ ፈለገ። ቲቲ ደግሞ በባዶ ግንድ ውስጥ ፈለገች። ከብዙ ፍለጋ በኋላ ኮኮ "ማንጎው የለም!" ብሎ በረጅሙ ተነፈሰ። "ወፍ ወስዳው ይሆን?" ስትል ቲቲ ጠየቀች። ኮኮ እራሱን ነቀነቀ። "በጣም ትልቅ ነው። በጣም ጠንካራዋ ወፍ እንኳ ልታነሳው አትችልም።" አለ። "ንፋስ ጥሎ ወስዶት ይሆን?" ስትል ቲቲ ጠየቀች። "ትናንት ማታ ምንም ንፋስ አልነበረም። ቅጠሎቹ አልተንቀሳቀሱም ነበር።" አለ ኮኮ። "ወይ ጉድ! ይህ በእውነት ትልቅ ምስጢር ነው።" አለች ቲቲ ግራ ሲገባት።

በዚያኑ ቅጽበት፣ የሜዳ አህያዋ ዛራ በሰፊው ሜዳ ላይ ስትጋልብ አዩዋት። ኮኮም "ዛራ! ዛራ!" ብሎ ጠርቶ "ማንጎዬን አይተሻል?" ሲል ጠየቃት። "ያንን ትልቁን ወርቃማ ማንጎ?" ስትል ዛራ ጠየቀች። "አዎ! እሱን ነው!" አለች ቲቲ። ዛራ ፈገግ በማለት "ትናንት አይቼው ነበር። በጣም የበሰለ እና የሚጣፍጥ ይመስል ነበር" አለች። "እባክሽ አሁን የት እንዳለ ታውቂያለሽ?" ሲል ኮኮ ጠየቃት። ዛራ ትከሻዋን በመነቅነቅ። "አላውቅም አዝናለሁ ኮኮ።" ስትል መለሰችለት።

ጓደኛማቾቹ ከዛፎች በስተጀርባ እና ከቁጥቋጦዎች በታች እያዩ ፍለጋቸውን ቀጠሉ። በአካባቢው ያለው ወራጅ ወንዝ ጋር ሲደርሱ ሊዮ የተባለ የአንበሳ ደቦል በውሃው ውስጥ እየተንቦራጨቀ ሲጫወት አገኙት። "እዚህ አካባቢ አንድ ግዙፍ ማንጎ አይተሃል?" ሲል ኮኮ ጠየቀው። ሊዮ ጭንቅላቱን እያወዛወዘ "አላየሁም... ግን ዛሬ ጠዋት በውሃው ላይ የሚንሳፈፍ ቢጫ ነገር አይቼ ነበር!" አላቸው። ኮኮ እና ቲቲ በደስታ ተያዩ። "ማንጎዬ መሆን አለበት!" አለ ኮኮ።

ኮኮ፣ ቲቲ እና ሊዮ በወንዙ ዳርቻ እየዞሩ ፈለጉ። ነገር ግን ማንጎውን ማግኘት አልቻሉም። የት ሊሆን ይችላል? እያለ ኮኮ መፈለጉን ቀጠለ። በአቅራቢያው ቢጫ ነገር ይታያችኋል? በማለት ጠየቃቸው። ፍየሏ ቲቲ ወደ አንድ ቦታ እያየች በድንጋጤ ጆሮዎቿ ቀጥ አሉ። "እዩ!" ስትል ወደ አንድ ትልቅ አረንጓዴ ቁጥቋጦ እየጠቆመች በሹክሹክታ ተናገረች።

ከቁጥቋጦው በስተጀርባ አንድ ትንሽ ዝሆን ተቀምጦ ነበር። በእግሮቹ ስር ... አንድ ግዙፍ፣ ወርቃማ ማንጎ ነበረ። ከየት አገኘኸው? ብሎ ኮኮ ዝሆኑን አፋጠጠው። ኮኮ ማንጎው መገኘቱ ደስ ቢለውም ዝሆኑ እጅ እንዴት ሊገባ እንደቻለ ግራ ገብቶታል። ትንሹ ዝሆን ስሙ ቶምቦ ይባላል — በፍርሀት ተውጦ ቀና ብሎ አያቸው። "እኔ... አ..." መልስ ለመስጠት ቢሞክርም ከፍርሃቱ የተነሳ የሚናገረው ጠፋበት።

"ከዛፉ ላይ ቀንጥሰህ ወስደህ ነው?" ሲል ኮኮ በንዴት ጠየቀው። ቶምቦ ቀስ ብሎ ራሱን ነቀነቀ። "ትናንት መሬት ላይ ብቻውን ወድቆ አገኘሁት። ባለቤቱ መጥቶ እስኪወስደው በጣም ጠበቅሁ፣ ግን ማንም አልመጣም፣ ስለዚህ እንዳይጠፋ ብዬ እዚህ ይዤው ተቀመጥኩ።" አለ ቶምቦ። ኮኮ በዝሆኑ መልካምነት በጣም ተገረመ። "እየሰረቅክ አልነበረም ማለት ነው?" ሲል ጠየቀ። ቶምቦ በበድጋሚ ራሱን ነቀነቀ። "አይደለም! እኔ በፍጹም አልሰርቅም። የማን ማንጎ እንደሆነ ስላላወቅኩ ነው እንጂ።" አለው።

ቲቲ "ሁሉም ነገር ትልቅ አለመግባባት ነበር" አለች። ቶምቦ በኩምቢው ግዙፉን ማንጎ በቀስታ ወደ ኮኮ በመግፋት "ይቅርታ!" አለ። ኮኮ የቶምቦን ያዘነ ፊት አይቶ... ይቅርታ ሊያደርግለት ወሰነ። "ችግር የለም ቶምቦ" አለ ኮኮ። ከዚያም ኮኮ ግዙፉን ማንጎ በደስታ እየተመለከተ... "ይሄ ማንጎ አንድ ዝንጀሮ ብቻውን ሊበላው በጣም ትልቅ ይመስለኛል።" "በእውነት?" ስትል ቲቲ ቅንድቧን ከፍ አድርጋ ጠየቀች። "ኑ እንሂድ ከዛፉ ስር ተጠልለን እንብላ" አለ ኮኮ።

ሁሉም በአንድ ላይ ተሰበሰቡ — ኮኮ፣ ቲቲ፣ ሊዮ፣ ዛራ እና ቶምቦ — በትልቁ የማንጎ ዛፍ ስር አብረው ተቀመጡ። ኮኮ ግዙፉን ማንጎ ወደ ጣፋጭ ወርቃማ ቁርጥራጮች ከፋፈለው። ለእያንዳንዱ ጓደኛ አዳረሰ። "እምምም" አለች ቲቲ ከንፈሯን እየላሰች። "ይህ እስከዛሬ ከቀመስኳቸው ማንጎዎች ሁሉ ምርጡ ነው" ስትል አደነቀች። "ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?" አለ ቶምቦ "ለምን?" ጠየቀ ኮኮ። "ምክንያቱም በጋራ ስለበላን ነው" አለ ቶምቦ። ሁሉም በመስማማት ጭንቅላታቸውን ነቀነቁ።

አምስቱ አዳዲስ ጓደኛሞች ሆዳቸው ጠግቦ በጥላው ስር አብረው ተቀመጡ፣ እጃቸው በማንጎው እየተጣበቀ በደስታ ተሞሉ። አንዲት ቁራጭ ማንጎ እንኳ አልቀረችም።

ሌሎች የኮኮ እና ቲቲ ታሪኮች ይቀጥላሉ2018 ዓ.ም